Posted on 2017-12-24
ITDB ታህሳስ 7/2017ዓ/ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ አዲስ ያለማውን www.aapdb.gov.et የተሰኘውን የከተማውን የገፀምድራዊ፣ ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ፕላን እንዲሁም የተለያዩ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን መረጃ ተደራሽ ለማድረግ፣ ለማስተዋወቅና ከተማዋን በዘመናዊ ፕላን መምራት የሚያስችል ደረጃውን የጠበቀ ዌብሳይት በማልማት ወደ ስራ እንዲያስገባ ለከተማው ፕላንና ልማት ቢሮ አስረክቧል።
በዚህም የርክክብ መርሃ ግብር ላይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ግሩም አብተው ለከተማው ስማርት ሲቲ ትግበራ የሚስማሙ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በማልማት የከተማዋን ዲፕሎማቲክ ማዕከልነት፣ ዓለማቀፍ ተወዳዳሪነትና ተመራጭነት እያሳደግን እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፕላንና ልማት ቢሮ የከተማ ጥናት፤ መረጃና አቅም ግንባታ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ኃይሌ የከተማው ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ የፕላንና ልማት ቢሮ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አገልግሎት እንዲሰጥ ከተቋማት ጋርም የሚያስተሳስር ሲስተም በተጨማሪነት በማልማት ተቋማዊ ትብብሩን እያጎለበተ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በርክክብ ሥነ ስርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ግሩም አብተው፣ ፕላንና ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ኃይሌ፣ የፕላንና ልማት ቢሮ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሲሳይ ተረፈ፣ የሁለቱም ተቋማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሮች የተገኙ ሲሆን ይህ ዌብሳይት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በሶስት ቋንቋዎች የተግባቦትና የህዝብ ግንኙነት ስራ በመስራት የከተማዋን የልማት ውጤቶች፣ ታላላቅ ፕሮጀክት ውጤቶች፣ የኮሪደር ልማቶች፣ የአካባቢ ልማትና የመሰረተ ልማት ፕላን ስራዎች በማስተዋወቅና ገፅታ በመገንባት ረገድ ከፍ ያለ አበርክቶ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።